የሶማሊ ክልል የእርሻ ልማት ቢሮ ለአርሶአደሮች በብድር የሚቀርቡ የእርሻ ትራክተሮችን ማስመጣቱን አስታወቀ
ጅግጅጋ ፤ ( የሶመብኤ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም) የሶማሊ ክልል የእርሻ ልማት ቢሮ ለአርሶአደሮች በብድር የሚቀርቡ 50 የእርሻ ትራክተሮችን ማስመጣቱን አስታውቋል።
በሶማሊ ክልል የእርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መካከል አርሶአደሮች ዘመናዊ የሰብል ልማት ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተጠቃሽ ነው።
በዚህ መሰረት ከለውጡ ወዲህ ለክልሉ አርሶአደሮች የእርሻ ትራክተሮችን በብድር በማቅረብ በክልሉ የእርሻ ሜካናይዜሽን ለማስፋፋት እና የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።
የዚህ ስራ አካል የሆኑትና በሶማሊ ክልል የእርሻ ልማት ቢሮ በኩል ተገዝተው ለክልሉ አርሶአደሮች በብድር የሚቀርቡ 50 የእርሻ ትራክተሮች ዛሬ ጅግጅጋ ከተማ ገብተዋል።
በሶማሊ ክልል የእርሻ ልማት ቢሮ የግብርና ኤክስቴሽን ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አህመድ መሀመድ በክልሉ ከለውጡ ወዲህ የእርሻ ሜካናይዜሽን እና የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 480 ትራክተሮችን በብድር ለአርሶአደሩ መቅረቡን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜ ቢሮው በብድር ለአርሶአደሩ የሚቀርቡ 50 ትራክተሮችን ማስመጣቱን ተናግረዋል።
ትራክተሮቹ በክልሉ በሚካሄዱ የሰብል ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራዎች የጎላ ጠቀሜታ ያበረክታሉ ያሉት ዳይሬክተሩ አርሶአደሮች 50 ከመቶ ክፍያ አስቀድመው በመክፈል የእርሻ ትራክተሮቹን በብድር መውሰድ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
